ኢትዮጵያ የነፃ ንግድ ቀጣናዎችን ውጤታማ ለማድረግ ከ10 በላይ ሕጎችና መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረጓ ተገለጸ
ኢትዮጵያ የነፃ ንግድ ቀጣናዎችን ውጤታማና ተወዳዳሪ ለማድረግ የልዩ ኢኮኖሚ ቀጣናዎች አዋጅን ጨምሮ ከ10 በላይ ሕጎችና መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረጓ ተገለጸ።
ተግባራዊ ከተደረጉ የሕግና የመመሪያ ማዕቀፎቹ መካከል የልዩ ኢኮኖሚ ቀጣናዎች አዋጅ፣ የገቢ ግብርና የጉምሩክ አሠራር ሥርዓቶችና መመሪያዎች፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የአሠራር ማኑዋሎች፣ የውጭና የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን የሚመሩ ሕጎችና የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ደንቦች ይገኙበታል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣቸው መመሪያዎችና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን (IPDC) የተዘረጉ የአሠራር ደንቦችና ሥርዓቶች የሕግና የቁጥጥር ማዕቀፉ አካል ናቸው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ አቶ ሰለሞን ደስታ የፋይናንስ አገልግሎት ልህቀት ለተወዳዳሪ ነፃ ንግድ ቀጠናዎች” ወርክሾፕ መዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ብሔራዊ ባንኩ የነፃ ንግድ ቀጣናዎችን አሠራር ለማሻሻልና በቀጣናዎቹ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ባለሀብቶች የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል።
ከተከናወኑት ተግባራት መካከል የውጭ ምንዛሬ ሥርዓት ማሻሻያ፣ በልዩ ኢኮኖሚ ቀጣናዎች ውስጥ ለሚሠሩ ባንኮች የወጣ መመሪያ እንዲሁም ከባንክ ወደ ባንክ ፈጣን የገንዘብ ዝውውርና የክፍያ ሥርዓት (Real-Time Gross Settlement – RTGS) ተግባራዊ መደረጋቸውን እንደ ዋና ዋና ማሳያዎች ጠቅሰዋል።
አቶ ሰለሞን አክለውም፣ በወርክሾፑ የተነሱ ሐሳቦችና የተለዩ የፋይናንስ አገልግሎት ክፍተቶች ወደ ፕሮፖዛል ተቀይረው በተግባር እንዲውሉ ለባንኮች የሥራ አቅጣጫ ሰጥተዋል።
ወርክሾፑ በፋይናንስ ተቋማትና በኢንቨስትመንት ልማት መካከል ያለውን ቅንጅት ለማጠናከር፣ በአገልግሎት አቅርቦት ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመለየትና በነፃ ንግድ ቀጣናዎች ለሚንቀሳቀሱ ባለሀብቶች የተሻለና ተደራሽ የፋይናንስ አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችሉ ተግባራዊ መፍትሔዎችን ለመለየት ዕድል መፍጠሩ ተጠቁሟል።