• Striving for eco industrial park
logo

የነፃ ንግድ ቀጠናዎችን ማጠናከር የኢትዮጵያን ገቢ ወጪ ንግድ ሉዐላዊነት እንደሚያረጋግጥ ተገለጸ

የነፃ ንግድ ቀጠናዎችን ማጠናከር የኢትዮጵያን ገቢ ወጪ ንግድ ሉዐላዊነት እንደሚያረጋግጥ ተገለጸ

በኢትዮጵያ የነፃ ንግድ ቀጠናዎችን ማጠናከር የኢትዮጵያን ገቢ ወጪ ንግድ ሉዐላዊነት ለማረጋገጥና በውጭ ሀገራት ላይ ያላትን ጥገኝነት ለመቀነስ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ።

ይህ የተገለጸው በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጋራ በድሬ ዳዋ ባዘጋጁት “የፋይናንስ አገልግሎት ልህቀት ለተወዳዳሪ ነፃ ንግድ ቀጣናዎች” በሚል መሪ ሐሳብ በተካሄደው ወርክሾፕ ላይ ነው።

በወርክሾፑ ላይ የኮርፖሬሽኑ የፋይናንስ አማካሪ አቶ ፍጹም ግርማ፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ለሀገራቸው የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እያበረከቱ ያሉትን አስተዋጽኦ በምሳሌነት ያቀረቡ ሲሆን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን፣ ከብሔራዊ ባንክ፣ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ከግል ባንኮች የተውጣጡ ፓናሊስቶች በቀረበው ሐሳብ ላይ ባንኮች ለነፃ ንግድ ቀጣናዎች ያላቸው ጠቀሜታና ለኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ባላቸው አስተዋጽኦ ላይ ውይይት ተደርጓል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍጹም ከተማ የሀገራዊ ተቋማትን ቅንጅት ማሻሻልና የነፃ ንግድ ቀጣናዎችን አቅም ማሳደግ ኢትዮጵያ በውጭ ሀገራት ላይ ያላትን ጥገኝነት ለመቀነስና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ወርክሾፑ በፋይናንስ ተቋማትና በኢንቨስትመንት ልማት መካከል ያለውን ቅንጅት ለማጠናከር፣ ያሉትን የአገልግሎት ክፍተቶች ለመለየትና በነፃ ንግድ ቀጣናዎች ለሚንቀሳቀሱ ባለሀብቶች የተሻለና ተደራሽ የፋይናንስ አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችሉ ተግባራዊ መፍትሔዎችን ለመለየት ዕድል ፈጥሯል።