በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሥራ አስጀመሩ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በሳም ፕሬሺየስ ሜታልስ መካከል በተደረገ አጋርነት በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና የተገነባው ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ ሥራ አስጀመሩ።
በዓመት ከ600 ቶን በላይ ውድ ማዕድናትን የማጣራት አቅም ያለው ፋብሪካው፣ በኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ የሀገር ውስጥ እሴት ጭማሪን ለማሳደግና ሀገሪቱን በውድ ማዕድናት ማጣራት ረገድ ቀጣናዊ ማዕከል ለማድረግ እንደሚያግዝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡
ፋብሪካው የሀገር ውስጥ ማዕድናትን በማጣራት እና ተጨማሪ እሴት በመፍጠር የወጪ ንግድ ገቢን ለማሳደግ፣ የሰለጠነ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የጌጣጌጥ ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ እንደሚጠቅም ተገልጿል።
በተጨማሪም የወርቅ እሴት ሰንሰለቱን ይበልጥ ግልጽና ተወዳዳሪ በማድረግ የማዕድን ሀብትን ወደ ኢንዱስትሪ ምርት የማሸጋገር ሂደትን ለማጠናከር ፋብሪካው ጠቃሚ ሚና እንደሚኖረው ይታመናል።
የፋብሪካው ሥራ መጀመር የኢትዮጵያን የማዕድን ሀብት በሀገር ውስጥ የማቀነባበር አቅም ለማሳደግ፣ የኢንዱስትሪ ልማትን ለማበረታታትና በዘርፉ የሚፈጠረውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ እንደ አንድ ትልቅ ምዕራፍ ይወስዳል።
የማጣሪያውን ግንባታ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ኮንስትራክሸን ቢዝነስ ልማት ዘርፍ ከአንድ አመት ባነሰ ጊዜ ገንብት ማስረከብ ችሏል፡፡