• Striving for eco industrial park
logo

የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ኢንቨስት ለማድረግ ከኮርፖሬሽኑ አመራሮች ጋር ተወያየ

የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ኢንቨስት ለማድረግ ከኮርፖሬሽኑ አመራሮች ጋር ተወያየ

በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ከ8 በላይ ሀገራት የተሰማራው የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ልዑካን ቡድን አባላት ግሩፑ ሀብቱንና የኢንዱስትሪ ልማት እውቀቱን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በሚተዳደሩ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ላይ ለማዋል ስለሚችልበት አግባብ ከኮርፖሬሽኑ አመራሮች ጋር ተወያይቷል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኦፕሬሽንና ፓርክ አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍጹም ከተማ፣ የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ልዑካን ቡድንን በኮርፖሬሽኑ ዋና መሥሪያ ቤት ተቀብለው አወያይተዋል።

በዚህም ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች የተዘረጉ የመሠረተ ልማት አውታሮች፣ የአገልግሎት አሰጣጦች እንዲሁም ለባለሀብቶች የሚደረጉ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን በተመለከተ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል።

የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ልዑካን ቡድን በበኩሉ፣ መቀመጫውን ናይጄሪያ ያደረገው ግሩፑ በብረታ ብረት ማምረት፣ በግንባታ ዕቃዎች፣ በኬሚካል፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በታዳሽ ኃይል፣ በሎጂስቲክስ እንዲሁም በጥናትና ምርምር ዘርፎች ላይ የተሰማራ መሆኑን ገልጿል።

ተቋሙ በ8 ሀገራት ከ35 በላይ የማምረቻ ኩባንያዎችን በማስተዳደር ላይ ሲሆን፣ በቀጣይም በኢትዮጵያ ሀብቱንና የኢንዱስትሪ ልማት እውቀቱን ለማዋል በትጋት እንደሚሠራ አረጋግጧል።