ከልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች የሚወጡ ተረፈ ምርቶችን ወደ አማራጭ የኃይል ምንጭ ለመቀየር የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከCO3 ኢነርጂ ኩባንያ ጋር ከልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች የሚወጡ ተረፈ ምርቶችን ወደ አማራጭ የኃይል ምንጭ በመቀየር ወደ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
የመግባቢያ ስምምነቱን በኮርፖሬሽኑ የኦፕሬሽንና ፓርክ አስተዳደር ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍጹም ከተማ እና የCO3 ኢነርጂ ፕሬዚዳንት ኤሪክ ፉስል ተፈራርመዋል።
አቶ ፍጹም ከተማ በስምምነቱ መሠረት በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች የሚወጡ ተረፈ ምርቶችን ወደ ሀብት በመቀየር ለተለያዩ አማራጮች መጠቀም እንደሚቻልና ይህም ትርፋማነትን ከማረጋገጥ ባለፈ ለአካባቢ ጥበቃ የራሱን አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም ኮርፖሬሽኑ ለሚከናወነው ሥራ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
በኮርፖሬሽኑና በኩባንያው የተፈረመው ስምምነት በሙከራ ደረጃ በሀዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የሚጀመር ሲሆን፣ ውጤታማነቱ ከተገመገመ በኋላ በሌሎች ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንደሚተገበር አቶ ፍጹም ገልጸዋል።
የCO3 ኢነርጂ ፕሬዚዳንት ኤሪክ ፉስል በበኩላቸው፣ ከኢንዱስትሪዎች የሚወጡ ተረፈ ምርቶችን ወደ ተለያዩ የኃይል አማራጮች የመቀየር ሥራ በተለያዩ አገራት ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ገልጸው፣ አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ እንዲሁም በአፍሪካ ገበያ ለማቅረብ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
በስምምነቱ መሠረት የሙከራ ሥራው በቀጣዮቹ ስድስት ወራት በሀዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ይካሄዳል። በሙከራው የሚገኘውን ውጤት በመገምገም፣ ከተረፈ ምርቶች ለትልልቅ ኢንዱስትሪዎችና ኩባንያዎች እንደ አማራጭ የኃይል ምንጭ ሊያገለግል የሚችል ምርት በማምረት ወደ ገበያ ለማቅረብ ታቅዷል።