ኮርፖሬሽኑ ከኢትዮጵያ ኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከኢትዮጵያ ኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ጋር በተለያዩ የልማት መስኮች በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት (MoU) ተፈራርሟል።
የመግባቢያ ስምምነቱን በኮርፖሬሽኑ በኩል የኦፐሬሽንና የፓርክ አስተዳደር ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍጹም ከተማ፣ በኢንስቲትዩቱ በኩል ደግሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሐሰን ሁሴን ፈርመዋል።
አቶ ፍጹም ከተማ በወቅቱ እንደገለጹት፣ ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን፣ ሥራ ፈጣሪዎችን እና አነስተኛና መካከለኛ አምራቾችን ለማበረታታት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በዚህም የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ 72 በመቶ መድረሱን አመልክተዋል።
አቶ ፍጹም አክለውም፣ የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ኮርፖሬሽኑ የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማፋጠን፣ አዳዲስ የንግድ ሀሳቦችን ለመደገፍ እና አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ለማሳደግ እየተከናወነ ያለውን ሥራ ይበልጥ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል። ከኢንስቲትዩቱ ጋር በትብብር መስራት ተጨባጭ ውጤቶችን ለማስመዝገብ እንደሚያግዝም ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሐሰን ሁሴን፣ ኢንስቲትዩቱ አዳዲስ የሥራ ፈጠራ ሀሳቦች ወደ ተግባር እንዲሸጋገሩና አነስተኛና መካከለኛ አምራቾች እንዲጠናከሩ በማስቻል ላይ እንደሚሰራ ገልጸዋል። የኮርፖሬሽኑ ተግባራት ከኢንስቲትዩቱ ተልዕኮ ጋር የሚጣጣሙ በመሆናቸው፣ በቀጣይም በጋራ በመስራት ለሀገር እድገት የሚበረክተውን አስተዋጽኦ የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
በተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት መሠረት፣ በኮርፖሬሽኑ በሚተዳደሩ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለተመረጡ አዳዲስ የንግድ ሀሳቦች የሥራ ቦታዎች፣ የማምረቻ ፋሲሊቲዎች እና የሎጂስቲክስ መሠረተ ልማቶችን ማመቻቸት፣ የስትራቴጂክ አመራርና ቁጥጥር መስጠት፣ እንዲሁም የሥልጠናና የንግድ ልማት አገልግሎቶችን በማስተባበር በትብብር እንደሚሰሩ ተገልጿል፡፡