ኮርፖሬሽኑ ከ26.7 ቢሊዮን ብር በላይ የተኪ ምርት በ2018 በጀት ዓመት ማምረቱን አስታወቀ
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በሚያስተዳድራቸው ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በ2018 በጀት ዓመት ከ26.7 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የተኪ ምርቶች ተመርተው ለሀገር ውስጥ ገበያ መቅረባቸውን የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።
ኮርፖሬሽኑ በሐዋሳ ከተማ ባካሄደው የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መሠረት፣ በበጀት ዓመቱ ከ27.5 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን የተኪ ምርቶች ለሀገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ ነበር። ከዚህ ውስጥ ከ26.7 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ምርት በኮርፖሬሽኑ በሚተዳደሩ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በሚገኙ ባለሀብቶች ተመርቶ ለገበያ መቅረቡን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ ለሀገር ውስጥ ገበያ የቀረቡት ምርቶች ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸሩ 44 በመቶ ዕድገት አስመዝግበዋል። ከልዩ የኢኮኖሚ ዞኖቹ መካከል ቦሌ ለሚ፣ አዳማ እና ደብረ ብርሃን ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች የሚገኙ ባለሀብቶች ከፍተኛውን የተኪ ምርት ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ ቀዳሚ ደረጃን መያዛቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ኩባንያዎች ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚያቀርቧቸውን ምርቶች ይበልጥ እንዲያሳድጉና የምርት አቅርቦቱም በቀጣዩ በጀት ዓመት በተመሳሳይ መልኩ እንዲቀጥል በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በሌላ በኩል፣ በበጀት ዓመቱ ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ከ152 በላይ ለሚሆኑ ድርጅቶች እና ከ5,800 በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች ዘላቂ የገበያ ትስስር መፍጠር መቻሉ ተገልጿል።
በተጨማሪም ኮርፖሬሽኑ በሚተዳደሩት ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ባሳየው የእድገት ጉዞ እስካሁን ከ100 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አምራቾችና አቅራቢዎች የገበያ ትስስር መፍጠር መቻሉም ተጠቅሷል።
በአርሶ አደሮች፣ በአምራቾችና በኩባንያዎች መካከል በተፈጠረው የገበያ ትስስር ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የንግድ ግብይት እንዲፈጸም ማስቻሉ ተገልጿል። ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 19 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን ሪፖርቱ ያሳያል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኮርፖሬሽኑ በሚተዳደሩ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ባሉ ባለሀብቶች ተመርተው ወደ ውጭ ገበያ ከተላኩ ምርቶች 266.9 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ንግድ ገቢ ተገኝቷል። በተጨማሪም ከ750 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የተመዘገበ የመነሻ ካፒታል ያላቸው 166 አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን መሳብ መቻሉ እንዲሁም 5.8 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱ ተቋሙ ያለውን እምቅ አቅም ወደ ተጨባጭ ሀገራዊ እድገት እየቀየረ መምጣቱን ያመለክታል።
3OEB30