• Striving for eco industrial park
logo

የኮምቦልቻ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን በሦስት ዘርፎች ዓለም አቀፍ እውቅና አገኘ

የኮምቦልቻ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን በሦስት ዘርፎች ዓለም አቀፍ እውቅና አገኘ

የኮምቦልቻ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን በጥራት ሥራ አመራር ስርዓት (ISO 9001:2015)፣ በአካባቢ ጥበቃ ሥራ አመራር ስርዓት (ISO 14001:2015) እና በሥራ ላይ ጤናና ደህንነት አስተዳደር ስርዓት (ISO 45001:2018) ከኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዓለም አቀፍ እውቅና አግኝቷል።  

የልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ ሥራ አስኪያጅ አህመድ ሰይድ እንደገለጹት፣ ይህ እውቅና የዞኑን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ከማሳደጉም በላይ ለባለሀብቶች ያለውን ተመራጭነት እንደሚያጠናክር ገልጸዋል። ለተገኘው ስኬትም አስተዋፅኦ ላበረከቱ ባለሙያዎች፣ አጋር ተቋማት እና ለመላው ሠራተኞች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

አስተዳዳሪው አክለውም፣ ይህ እውቅና በቴክኖሎጂ የተደገፈ መሠረተ ልማትን ማስፋፋት፣ የአገልግሎት ቅልጥፍናና ጥራትን ማሻሻል እንዲሁም የዞኑን የሥራ አፈጻጸም የበለጠ እንዲጠናከር እንደሚያስችል ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሚያስተዳድራቸውን ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች እና ኢንዱትሪ ፓርኮች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማጠናከር የተለያዩ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ለማሟላት ሲሠራ ቆይቷል።

በዚህም መሠረት የሀዋሳ፣ የቦሌ ለሚ፣ የአዳማ እና የኮምቦልቻ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች እነዚህን ዓለም አቀፍ እውቅናዎች ያገኙ ሲሆን፣ የኮርፖሬሽኑ ዋና መሥሪያ ቤት እና የደብረ ብርሃን ልዩ ኢኮኖሚ ዞንም ተመሳሳይ እውቅና ለማግኘት መደስፈርቶችን የማሟላት ሥራዎች በመካሄድ ላይ ናቸው።

ኮርፖሬሽኑ እነዚህን ዓለም አቀፍ መስፈርቶች በማሟላት በዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ምህዳር ውስጥ ያለውን ተወዳዳሪነት ለማጠናከር እና ለባለሀብቶች የተሻለ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚችል ያምናል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኮምቦልቻ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ጨምሮ 14 ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖችንና ኢንዱስትሪ ፓርኮችን የሚያስተዳድር የመንግሥት የልማት ተቋም ሲሆን በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች እና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ከ300 በላይ ባለሀብቶች የሚንቀሳቀሱ ሲሆን፣ እነዚህ ባለሀብቶች ከ100 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።