• Striving for eco industrial park
logo

ቂሊንጦ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የማምረቻ ቦታ የተሰጣቸው ኢንተርፕራይዞች በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡ ጥሪ ቀረበ

በቂሊንጦ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የማምረቻ ቦታ የተሰጣቸው ኢንተርፕራይዞች በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡ ጥሪ ቀረበ

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) በቂሊንጦ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የማምረቻ ቦታ በነጻ የተሰጣቸው ኢንተርፕራይዞች በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡ ጥሪ አቀረቡ፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው ከአነስተኛ እና ጥቃቅን ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ በመሸጋገር ሂደት ላይ ያሉ ኢንተርፕራይዞችን ለመደገፍ በማሰብ ኮርፖሬሽኑ አዲስ የአሰራር ስርዓት ተግባራዊ ማድረጉን አውስተው በዚህም ኮርፖሬሽኑ ከሚያስተዳድራቸው 14 ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች እና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ አንዱ በሆነው በቂሊንጦ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የማምረቻ ቦታ ለአራት አመት ያህል ጊዜ በነጻ ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ኢንተርፕራይዞችን ወደ ሂደቱ ለማስገባት ሲል የማምረቻ ቦታ ለአራት አመት በነጻ ከማቅረብ በተጨማሪ የኢንተርፕራይዞቹን እድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥ አምራቾቹ የተሰጣቸው ጊዜ ከተጠናቀቀ በኋላ የሚከፍሉት የሊዝ ክፍያ ላይ 40 በመቶ ቅናሽ መደረጉንም አብራርተዋል፡፡

የአንድ ሉአላዊ ሀገር የኢንዱስትሪ መሰረት መገንባት ያለበት በሀገሬው ዜጋ መሆኑን ያወሱት ዶ/ር ፍሰሃ ይታገሱ ይህንኑ መሰረታዊ ሀሳብ እውን ለማድረግ በማሰብ ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳራቸው ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ማእከላት ውስጥ ሀገር በቀል ተቋማት እንዲገቡ የተለየዩ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ወደ ቂሊንጦ ልዩ ኢከኖሚ ዞን እንዲገቡ የተመረጡ አምራች ኢንተርፕራይዞችም ይህንኑ ሀገራዊ ተልዕኮ ተገንዝበው በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ አነስተኛና መካከለኛ አምራቾችን ለማበረታታት በቂሊንጦ እና ቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ ከ26 በላይ አምራቾችን በውድድር በመለየት ከ10 ሄክታር በላይ መሬት በመጀመሪያው ዙር ያስተላለፈ ሲሆን በቀጣይም ለሌሎች ለማስተላለፍ በዝግጅት ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ልማት ኮርፖሬሽን አልምቶ በሚያስተዳድራቸው 14 ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ማዕከላት ውስጥ ከ300 በላይ ኢንቨሰተሮች ያሉ ሲሆን 60 በመቶ የሚሆኑት ባለሀብቶች ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ ቀሪዎቹ 40 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የውጩ ሀገር ዜጎች ናቸው፡፡ እነዚህ ባለሀብቶች መቶ ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡