የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ሚና ከፍ እንዲል በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ
ግብርና መር የሆነውን የሃገራችን ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት ውስጥ በመላው ሃገሪቱ በሚያስተዳድራቸው 14 የኢንቨስትመንት ማእከላቱ ውስጥ የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ በትኩረት በመስራት ላይ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሸን ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ ፍፁም ከተማ ገለፁ።
ምክትል ስራ አስፈፃሚው ይህን የገለፁት በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ውስጥ በአመት ከ4 ቢሊዮን በላይ ቆርኪዎችን በማምረት ለሃገር ውስጥ ገበያ የሚያቀርብ ጵንኤል ኢንዱስትሪ የተሰኘ ሃገር በቀል ኩባንያ ምረቃ በተካሄደበት ወቅት ነው።
ኮርፖሬሽኑ የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ተበረታተው ኢንዱስትሪውን እንዲመሩና የሃገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ የራሳቸውን አሻራ እንዲያሳርፉ ለማድረግ በከፍተኛ ሁኔታ እየሰራ መሆኑን የገለፁት አቶ ፍፁም አሁን ላይ ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ኢንቨስትመንት ማእከላት ውስጥ ከሚገኙ ባለሃብቶች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት ሃገር በቀል ድርጅቶች መሆናቸውን ገልፀዋል።
የጵንኤል ኢንዱስትሪ ባለቤትና ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ት ብርቱካን አበበ በበኩላቸው ኩባንያቸው ወደ ስራ ለማስገባት ለተሳተፉ ባለድርሻ አካላትና የመንግስት አካላት ምስጋናቸውን አቅርበው አሁን ላይ በሃገር ውስጥ ያለውን የቆርኪ ፍላጎት 80 በመቶ ፍላጎቱን ለመሽፈን መታቀዱን ገልፀዋል፡፡
በ1.7 ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ወደ ስራ የገባው ጵንኤል ኢንዱስትሪ በአመት 4 ቢሊዮን ቆርኪዎችን የሚያመርትና ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል የሚፈጥር ሲሆን በኮርፖሬሽኑ የኢንቨስትመንት ማእከላት ውስጥ በሴት ባለሃብት የሚመራ የመጀመሪያው ሃገር በቀል ድርጅት ነው፡፡