• Striving for eco industrial park
logo

የተለያዩ ሃገራት ዲፕሎማቶችና አምባሳደሮች በአዲስ አበባ የሚገኙ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን ጎብኙ

የተለያዩ ሃገራት ዲፕሎማቶችና አምባሳደሮች በአዲስ አበባ የሚገኙ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን ጎብኙ

በአዲስ አበባ ተቀማጭነታቸውን ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ ያሉ የልማት እንቅስቃሴዎችን፣ የኩባንያዎችን የሥራ ሂደት ተመልክተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር ባዘጋጁት በዚህ የጉብኝት መርሃ ግብር ላይ ቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን፣ የቂሊንጦ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን፣ እንዲሁም የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጅ ፓርክን ጎብኝተዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኦፐሬሽንና ፓርክ አስተዳደር ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍጹም ከተማ ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡና አምባሳደሮች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ ለዝግጅቱ መሳካት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ለኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምስጋና አቅርበዋል።

አቶ ፍጹም በንግግራቸው ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት በመላው ኢትዮጵያ 14 ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን እና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እያለማና እያስተዳደረ መሆኑን ጠቅሰው እነዚህ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ማዕከላት ኢንቨስትመንትን፣ ኢንዱስትሪያላይዜሽንን፣ የኤክስፖርት እድገትን፣ተኪ ምርት ማምረትን፤ የቴክኖሎጂ ሽግግርን እና የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማበረታታት ታስበው የተገነቡ ናቸው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የአይሲቲ ፓርክን ጨምሮ በእነዚህ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ከ300 በላይ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙና ከ100,000 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል።

የዛሬው የቦሌ ለሚ፣ የቂሊንጦ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እና የአይሲቲ ፓርክ ጉብኝት ለዲፕሎማቶቹ በኢንቨስትመንት ሥነ ምህዳሩ ውስጥ ስላሉት ዕድሎችና ቀጣይ ዕድገቶች አጭር ግንዛቤ ያስጨበጠ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ይህ ዓይነቱ ትብብር አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ለሚገኙ ባለሀብቶች የሚደረገውን ድጋፍና አጋርነት ለማጠናከር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አስገንዝበዋል።

በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉት አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዘርፍ እያደረገች ያለው እንቅስቃሴ ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ መሆኑንና በተለይም ልዩ የኢንኮኖሚ ዞኖች የተለያዩ ሀገራት ባለሀብቶችና አልሚዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያነሳሱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ዲፕሎማቶቹ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አልምቶ ከሚያስተዳድራቸው ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች በተጨማሪ በግል ባለሃብቶች የለሙ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጎብኝተዋል፡፡