የአውሮፓ ህብረት ቢዝነስ ልዑካን ቡድን አባላት ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን ጎበኙ
የአውሮፓ ህብረት–ኢትዮጵያ የቢዝነስ ፎረም ተሳታፊ የነበሩ የቢዝነስ ልዑካን ቡድን አባላት የቦሌ ለሚ እና ቂሊንጦ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን ጎብኝተዋል።
የልዑካን ቡድኖቹን የቂሊንጦ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቶሎሳ በዳዳ እና የቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ትንሳኤ ይማም አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን፤ በዞኖቹ ያሉ መሠረተ ልማቶችና የኢንቨስትመንት እድሎች፣ እንዲሁም የባለሃብቶችን የስራ እንቅስቃሴና በተለያዩ ዘርፎች የሚሰጡ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በተመለከተ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ለሁለት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ በተካሄደውና ከተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት የተውጣጡ ባለሀብቶችና የቢዝነስ ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ተሳትፎ በማድረግ፣ ኮርፖሬሽኑ በስሩ ስለሚያስተዳድራቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ያሉትን የኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎች አስተዋውቋል።
ከሚያዝያ 12 እስከ 13/2018 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል በተካሄደው የቢዝነስ ፎረም ለታደሙ የቢዝነስ ልዑካን አባላት፤ በኮርፖሬሽኑ ስር በሚተዳደሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ኢንቨስት በሚያደርጉበት ጊዜ ሊያገኟቸው ስለሚችሉት የኢንቨስትመንት ጥቅማጥቅሞችና ማበረታቻዎች እንዲሁም መሰረተ ልማቶች ዙሪያ በኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አማካሪ አቶ አለማየሁ ሰይፉ አማካኝነት ሰፊ ገለጻ ተደርጓል።
ኮርፖሬሽኑ በፎረሙ ላይ በነበረው ቆይታ የቡዝ ላይ ፕሮሞሽን፣ የቢዝነስ ለቢዝነስ (B2B) የጎንዮሽ ውይይቶች እና አጠቃላይ የኢንቨስትመንት አቅም የሚያሳይ ገለጻ በማቅረብ ለተሳታፊ ባለሃብቶች የማስተዋወቅ ተግባራትን አከናውኗል።