• Striving for eco industrial park
logo
  • by ipdcadmin
  • 0Comments
  • 11 hours, 27 minutes ago
  • 20 Views

የአዳማ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ዓለም አቀፍ እውቅና አገኘ

የአዳማ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ዓለም አቀፍ እውቅና አገኘ

የአዳማ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን በጥራት ስራ አመራር ስርዓት (ISO 9001:2015) እና በአካባቢ ጥበቃ ስራ አመራር ስርዓት (ISO 14001:2015) ከኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዓለም አቀፍ እውቅና አግኝቷል።

በእውቅና አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍፁም ከተማ እንደገለጹት፣ የእውቅናው መገኘት ኮርፖሬሽኑ በዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ውድድር ውስጥ ተወዳዳሪነቱን ለማጠናከርና ለባለሀብቶች የተሻለ የአገልግሎት ሁኔታ ለመፍጠር የሚያግዝ ነው።

አቶ ፍፁም አክለውም፣ ኮርፖሬሽኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖቹ የISO የሥራ አመራር ስርዓቶችን ለመተግበር በተከታታይ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው፣ ከሀዋሳና ቦሌ ለሚ በመቀጠል አዳማ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን እውቅናውን ማግኘቱን ጠቅሰዋል። በቀጣይም ኮምቦልቻን ጨምሮ ሌሎች ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖችና የኮርፖሬሽኑ ዋና መስሪያ ቤት ተመሳሳይ እውቅና እንዲያገኙ ሥራ በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፣ እውቅናው በዞኑ የሚገኙ ባለሀብቶች ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪና ተቀባይነት ያላቸው እንዲሆኑ ያግዛል። ሆኖም ሰርተፍኬቱን ማግኘት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ፣ የISO መስፈርቶችን በቀጣይነት በመተግበርና በየዓመቱ የሚካሄደውን የኦዲት ሂደት በተሳካ ሁኔታ በማለፍ ደረጃውን ማስጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት የዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ አቶ ተኬ ብርሃነ በበኩላቸው፣ የተሰጠው የISO ሰርተፍኬት የአዳማ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን በጥራትና በአካባቢ ጥበቃ ዘርፎች ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን የሚያሟላ የአሰራር ስርዓት መዘርጋቱን የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል። እውቅናው የተሰጠውም በሰነድ ግምገማና በቦታው በተካሄደ የሳይት ኦዲት ውጤት መሰረት መሆኑን አብራርተዋል።

የአዳማ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጉልላት አበበ በበኩላቸው እውቅናው የዞኑን የገበያ ተወዳዳሪነት እንደሚያሳድግ ገልጸው፣ ለስኬቱ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለሙያዎች፣ አጋር ተቋማትና ለሁሉም ሰራተኞች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ ለእውቅናው ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለሙያዎችና አጋር አካላት የምስጋና ምስክር ወረቀቶች ተበርክቶላቸዋል።