በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና የሚታየው ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገልጿል
ቋሚ ኮሚቴው በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና በሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚታየው ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን አሳውቋል።
ቋሚ ኮሚቴው የነፃ ንግድ ቀጠናውን ወቅታዊ የስራ እንቅስቃሴ ተዟዙሮ የተመለከተ ሲሆን በምልከታው ወቅት ከስራ ዕድል ፈጠራ፣ ከውጭ ምንዛሪ ግኝት፣ ተኪ ምርትን ከማምረት፣ ከቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ያለው ትስስር የሚበረታታ መሆኑ ተገልጿል።
ነፃ ንግድ ቀጠናው ለባለኃብቶች አስፈላጊ መሠረተ-ልማቶችን ከማቅረብ ጀምሮ የንግድ እንቅስቃሴውን ለማሳለጥ የሚረዱ የጉምሩክ፣ የኢሚግሬሽን፣ የባንክ፣ የስራ ፍቃድ፣ የጭነት ማስተላለፍ እና የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል አገልግሎት ስር እንዲሰጡ መደረጉ የሚበረታታ መሆኑም ተቀምጧል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በምልከታቸው ወቅት የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከሚያስገኘው ከፍተኛ የውጭ ሀገር ምንዛሪ በተጨማሪ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማረጋገጥ እንዲሁም በፓርኩ አካባቢ ለሚገኙ ማኅበረሰቦች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ድጋፎችን ከማድረግ አኳያ እየተከናወኑ ያሉ አበረታች ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
በመጨረሻም ቋሚ ኮሚቴው በንግድ ቀጠናው ከሚሰሩ ባለሙያዎች፣ ከሰራተኛ ተወካዮች እና አመራሮች ጋር ፍሬያማ ውይይት ያደረገ ሲሆን በንግድ በቀጠናው ከሚገኙ ባለኃብቶች ጋር በዘርፉ በሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ተነጋግረዋል።