የኢንዱስትሪ ልማትን ያለ ኤሌክትሪክ ልማት ማሰብ መኪናን ያለ ሞተር እንደ ማሰብ ነው - ዶ/ር ፍሰሃ ይታገሱ
የኢንዱስትሪ ልማትን ከኤሌክትሪክ ልማት ለይቶ ማሰብ መኪናን ያለ ሞተር እንደ ማሰብ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ፍሰሃ ይታገሱ ገለጹ።
ዶ/ር ፍሰሃ ይህን የገለጹት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በቂሊንጦ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ ያስገነባውን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያ በማስመረቅ ወቅት ነው።
እንደ ዶ/ር ፍሰሃ ገለጻ፣ ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ የኤሌክትሪክ መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች እየተስፋፉ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር ያለው ትብብር ለዘርፉ ዕድገት ወሳኝ ነው።
የኢንዱስትሪ ልማትና የኤሌክትሪክ ልማት እጅና ጓንት ሆነው አብረው ማደግ እንዳለባቸው ያስታወቁት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ልማት ግቦች ለማሳካት የኃይል መሠረተ ልማት መጠናከር ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
በተጨማሪም ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ፓርኮችና ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት የሚሰጡ አሠራሮችን ተግባራዊ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸው፣ የተመረቀው የቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያም ከዚህ ጥረት ጋር የሚጣጣም መሆኑን አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት የሚገኙ ተሽከርካሪዎች ውስጥ 10 በመቶ ያህሉ የኤሌክትሪክ መኪኖች መሆናቸውን የጠቀሱት ዶ/ር ፍሰሃ፣ ወደፊትም በሌሎች ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ተመሳሳይ የቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎች እንደሚገነቡ ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው፣ 24 የኤሌክትሪክ መኪኖችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚችለው ይህ የቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር በትብብር መገንባቱን ገልጸዋል።
ኢንጂነር ጌቱ እንዳሉት፣ ተቋሙ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች 40 የሚደርሱ የቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎችን ለመገንባት 10 ሚሊዮን ዶላር መድቦ በተግባር ላይ ይገኛል። በቂሊንጦ የተገነባው ጣቢያም በአዲስ አበባ የተገነባው አራተኛው የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያ መሆኑን ገልጸዋል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ በሪሶ ሀሰን በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ወደ ኤሌክትሪክ ትራንስፖርት ስትሸጋገር የቻርጅ ማድረጊያ መሠረተ ልማት እጥረት ዋነኛ ፈተና እንደነበር ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ብቻ ከ200 በላይ የቻርጅ ማድረጊያ ቦታዎች መኖራቸውን አስታውቀዋል።
አገልግሎቱ በተጀመረበት አጭር ጊዜ የተመዘገበው ውጤት አበረታች መሆኑን የገለጹት አቶ በሪሶ፣ በአዲስ አበባ ብቻ ከ1,700 በላይ የቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎች እንደሚያስፈልጉ ጠቁመዋል።
በመጨረሻም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ይህንን ሀገራዊ ተልዕኮ በጋራ ለማሳካት እየሠሩ መሆናቸው የሚበረታታ እንደሆነ ገልጸው፣ ኢትዮጵያ ከኤሌክትሪክ መኪና አስመጪነት ወደ አምራችነትና ወደ ውጭ ገበያ ላኪነት ለመሸጋገር የሁለቱ ተቋማት ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን አስምረውበታል።