• +251118722266
  • Striving for eco industrial park
logo
  • by admin
  • 0Comments
  • 1 year, 5 months ago
  • 577 Views

የኢንዱስትሪ ፓርኮችና የአርሶ አደሮች የገበያ ትስስር

በመላው ሃገሪቱ በተገነቡት ኢንዱስትሪ ፓርኮች በተፈጠረ የገበያ ትስስር ከ300ሺ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተገለጸ፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የማርኬቲንግና ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘመን ጁነዲን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት በመላው ሃገሪቱ በተገነቡት የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮች የግብርና ምርቶቻቸውን በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ላሉ አምራቾች እንዲያቀርቡ በማድረግ ሰፊና ዘላቂ የገበያ ትስስር በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በገበያ ትስስሩ ከ 15,000 በላይ አርሶ አደሮች በጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአቮካዶ ዘይት ምርት በማምረት ለተሰማራ ኩባንያ የአቮካዶ ፍራፍሬ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ኃላፊው በደብረ ብርሃን እና ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ደግሞ ለቢራ አምራች ካምፓኒዎች ብቅል የማቅረብ ስራ ለሚሰሩ አምራቾች የቢራ ገብስ በማቅረብ በኩል ከ280,000 በላይ አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ ስራዎችን በመሰራት ላይ እንደሚገኙ የገለጹት አቶ ዘመን በቅርቡም በአፋር አካባቢ ያለውን የግመል ወተት በግብዓትነት የሚጠቀም ካምፓኒ በሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲሁም አማራ ክልል አካባቢ ያለውን የበቆሎ ምርት በግብዓትነት የሚጠቀም አምራችም እንዲሁ በባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብተው ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ፈጽመው ግንባታ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተልባ እግርን በግብዓትነት የሚጠቀም ካምፓኒ ጋር የገበያ ትስስር ስራዎች ለመስራት የዘር ብዜትና የምርምር ስራዎች በመሰራት ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ኃላፊው በቀጣይም የዘር ብዜቱን ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት በስፋት ወደ ምርት እንዲገቡ የማድረግ ስራዎች እንደሚሰሩ አብራርተዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች በአልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ፤በአግሮ ፕሮሰሲንግ፤በፋርማሲዩቲካል ዘርፎች ተሰማርተው እንደሚገኙ የገለጹት አቶ ዘመን በተለይም ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ ያለው የኢንቨስትመንት ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ መነቃቃቱንና የባለሃብቶች ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎትም በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በኮርፖሬሽኑ አሁን ላይ 11 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሙሉ በሙሉ በስራ ላይ የሚገኙ ሲሆን የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክን ወደ ስራ ለመመለስም የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን የተናገሩት አቶ ዘመን በተለይም ፓርኩን ወደ ነበረበት ለመመለስ የነበሩ ባለሃብቶችን የማወያየት እና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ መድረስ መቻሉን አቶ ዘመን ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡