ደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ!
መንግስት ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የሚያግዙ 11 ኢንዱስትሪ ፓርኮችና 1 ነፃ የንግድ ቀጣና በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች አልምቶ ወደ ሥራ በማስገባት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ የስራ እድል ፈጠራን በማጠናከር እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማቀላጠፍ በኩል የበኩላቸውን ሚና በመወጣት ላይ ይገኛሉ፡፡
ሃገራችንን ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሻገር ታቅደው ከለሙ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አንዱ ከአዲስ አበባ በ130 ኪሎሜትር ርቀት በደብረ ብርሃን ከተማ ይገኛል።
ፓርኩ እ.ኤ.አ በ2019 ስራ የጀመረ ሲሆን በ100 ሄክታር መሬት ስፋት ላይ 8 የፋብሪካ ሼዶችን በመገንባት አልሚዎች ቀጥታ ወደ ፓርኩ ገብተው ማሽኖቻቸውን ወይም ማምረቻቸውን ተክለው በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ እንዲገቡ ታሳቢ ተደርጎ የተገነባ ነው።
የማምረቻ ሼዶቹ ባለ 5500 ካሬ ሜትር ስፋት ሲኖራቸው የውሃ፣ የመብራት፣ የቴሌኮም አገልግሎትና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ የፍሳሽ መስመሮች ዝርጋታ እንዲሁም አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች ተሟልቶላቸው 8 ባለሃብቶች በስራ ላይ የሚገኙ ሲሆን በአልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ እንዲሁም ብቅል በማምረት ዘርፍ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡
በፓርኩ ኢንቨስት ያደረጉ አልሚዎች የኢንቨስትመንት ካፒታላቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ የተለያየ ቢሆንም በ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 9 ወራት ብቻ ከ3.2 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የሚያወጡ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ችለዋል፡፡
በቀጣይ በፓርኩ የለማ መሬት በመረከብ ሼድ ገንብተው ለመስራት ፍላጎት ያላቸውን ባለሃብቶች ለማስገባት 35 ሄክታር የለማ መሬት አስፈላጊውን መሰረተ ልማት በማሟላት የተዘጋጀ ሲሆን አቅም ያለው የሃገር ልጅ ሁሉ መጥቶ በመስራት ትርፋማ እንዲሆኑ ሲል ኮርፖሬሽኑ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
በኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን ፀኃይ አትጠልቅም!
ይምጡ በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ በተገነቡት ኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን ኢንቨስት አድርገው ትርፋማ ይሁኑ!