ኮርፖሬሽኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ደህንነት በማስጠበቅ የኢንቨስተሮችን ትርፋማነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ነው
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በፓርኮች ጥበቃ፣ የደህንነትና የፀጥታ ስራዎች የዳሰሳ ጥናት ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡
የመግባቢያ ስምምነት ሰነዱን የተፈራረሙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ሃብት አስተዳደር ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አዲሱ ማሞ እና የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ፣የማማከር እና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሲሳይ ዘለቀ ናቸው።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ሃብት አስተዳደር ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አዲሱ ማሞ የፊርማ ስነ-ስርዓቱን ባከናወኑበት ወቅት የጋራ ስምምነቱ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለውን የኢንቨስትመንት ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ ለመጨመርና ለኢንቨስተሮች ምቹና ደህንነቱ የተጠበቀ የስራ ከባቢ እንዲኖር ለማድረግ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
አቶ አዲሱ በተጨማሪም በጥናት ሰነዱ ግኝት ላይ የሚታዩ ጥንካሬዎችንና ድክመቶችን በመለየትና በፓርኮች ምቹ የስራ ከባቢ እንዲኖር በማድረግ በኩል የፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ያለውን የረጅም ግዜ ልምድ ለስምምነቱ ውጤታማነትና የባለሃብቶችን ትርፋማነት ለማሳደግ የራሱ ድርሻ አለው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የምርምር፣ የማማከር እና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሲሳይ ዘለቀ በበኩላቸው ከኮርፖሬሽኑ ጋር የመስራት እድሉን በማግኘታቸው በተቋማቸው ስም አመስግነው የጥናት ስራው በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ስኬታማ እንዲሆን በጋራ የሚሰራ ይሆናል ብለዋል፡፡
በፓርኮች ሰላም፣ ጥበቃና ደህንነት ላይ ትኩረቱን የሚያደርገው ጥናት በቦሌ ለሚ እና አዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በሙከራ ደረጃ የሚጀመር ሲሆን በቀጣይ ሁለት ወራትም የመጀመሪያውን ምዕራፍ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል፡፡
ከዚህ ቀደም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች በቅንጅት ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።