ኢትዮጵያ በ2023 ከሰሃራ በታች የአፍሪካ አገራት ሦስተኛ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት እንደምትሆን አይ.ኤም.ኤፍ ተነበየ
በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ 156 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት በማስመዝገብ በፈረንጆቹ 2023 ከሰሃራ በታች ሦስተኛ ግዙፍ የኢኮኖሚ ባለቤት አገር እንደምትሆን ትንበያው አመልክቷል።
ቀደም ሲል የኢትዮጵያን አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት 126 ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን ያስቀመጠው የአይ.ኤም.ኤፍ ትንበያ ዳግም ሲከለስ ወደ 156 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ከፍ እንዲል አስችሎታል።
ናይጄሪያ በ 506 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ቀዳሚ ስትሆን ደቡብ አፍሪካ ደግሞ በ 399 ቢሊዮን ዶላር ትከተላለች።
ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቷ እኤአ እስከ 2028 መጨረሻ በማስቀጠል ይህን ደረጃዋን ተቆናጣ እንደምትዘልቅ የአይ.ኤምኤፍ ትንበያ ያሳያል።
በዚህም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገንብቶ የሚያስተዳድራቸው 11 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ብሎም በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ጉልህ ሚና እንደሚጫወቱ ይጠበቃል።
እንደ ቢዝነስ ዴይሊ ዘገባ ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ የተሻሉ አገራት መሆናቸው የተመላከተ ሲሆን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንም ባለፉት ሰባት አመታት ዘርፈ ብዙ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ ከ1.1 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የውጪ ምንዛሪ ማስገኘት ችሏል።
ኮርፖሬሽኑ ቀጥተኛ የውጪ ኢንቨስትመንትን በመሳብ የውጪ ምንዛሪ ግኝትን በመጨመር እና የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር በማድረግ ከፍተኛ የሆነ የስራ እድል መፍጠር፣ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማቅረብ ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጪ ምንዛሪን ማዳንና ነፃ ንግድ ቀጠናዎችን ማስፋፋት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።