ኮርፖሬሽኑ ያሉትን የኢንቨስትመንት አማራጮች በ"ኢንቨስት ኢን ኢትዮጵያ" ፎረም ላይ እያስተዋወቀ ነው
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን “ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ዝግጁ ነች” በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ በመሳተፍ ላይ ይገኛል፡፡
ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ የጀመረው "ኢንቨስት ኢን ኢትዮጵያ" የተሰኘው ፎሬም በየአመቱ በኢትዮጵያ ኢንቨትመንት ኮምሽን የሚዘጋጅ ሲሆን ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ መዘጋጀቱ ነው።
በፎረሙ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የጣሊያን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያ ትሪፖዲ እና ባለሀብቶች ተገኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ ኢትዮጵያ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን እየሰራች መሆኗን ገልጸዋል።
ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚቆየውን ፎረም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ስፖንስር ያደረገ ሲሆን ኮርፖሬሽኑ የሚያስተዳድራቸውን 14 ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለተሳታፊዎች እያስተዋወቀ ይገኛል።
በኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ከመንግስት ባለስልጣናት በተጨማሪ የኩባንያ ባለቤቶች፣ የኢንቨስትመንት አማካሪዎች እና የንግድ ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡
መድረኩ ኢትዮጵያ ያሏትን የኢንቨስትመንት አማራጮች ለዓለም ገበያ በማስተዋወቅ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ሀብትና እውቀታቸውን ስራ ላይ እንዲያውሉ ለማስቻል መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል፡፡