የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ እድገት ዘላቂ መሰረት እንዲኖረው አነስተኛና መካከለኛ አምራቾችን በልዩ ሁኔታ መደገፍ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ዘላቂ መሰረት እንዲኖረውና ለሃገር የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ለማሳደግ አነስተኛና መካከለኛ አምራቾችን በልዩ ሁኔታ መደገፍ እንደሚገባ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኦፕሬሽን እና ፓርክ አስተዳደር ዘርፍ ስራ አስፈጻሚ ፍጹም ከተማ ገለጹ፡፡
ስራ አስፈጻሚው ይህን የገለጹት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በሚያስተዳድራቸው ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ አነስተኛና መካከለኛ አምራቾችን በልዩ ሁኔታ ደግፎ እድገታቸውን ለማፋጠን በተመቻቸ ፕሮግራም ላይ እንዲሳተፉ ከተመለመሉ አነስተኛና መካከለኛ አምራቾች ጋር በተደረገ ውይይት ላይ ነው፡፡
ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ገብተው እንዲሰሩ ለማድርግ አቅዶ ሲሰራ የቆየ ሲሆን በእድሉ አነስተኛ ጥቃቅን ተቋማት እንዲሳተፉ ማስታወቂያ አውጥቶ ከ300 በላይ ከሚሆኑ ኢንተርፕራይዞች ፕሮፖዛል የተቀበለ ሲሆን ቀደሞ በተለዩ መመዘኛዎችን መሰረት በማድረግ የምልመላ ስራዎች ሲከናወን መቆየቱን ስራ አስፈጻሚው አስታውሰዋል፡፡
ከተመዘገቡት ኢንተርፕራይዞች መካከልም መመዘኛ መስርፈርቶችን መሰረት በማድረግ ከ50 በላይ ኢንተርፕራይዞችን የፕሮጀክት ፕሮፖዛል ግምገማ እና የመስክ ምልከታ በማድረግ በኤክስፖርትና በተኪ ምርት የተሻለ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ተብለው የተለዩ 26 አምራቾች ተለይተው በተለያዩ ዘርፎች ለማሰማራት የሚያስችል ስራዎች ሲሰሩ መቆየቱን አቶ ፍጹም ከተማ አብራርተዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተለዩትን አምራቾችን ወደ ስራ ለማስገባት 10 ሄክታር መሬት ከተለያዩ ማበረታቻዎች ጋር ማቅረቡንም ጠቁመዋል፡፡
አሁን የተለዩትን ኢንተርፖራይዞች ወደ ስራ አስገብቶ የሚያስመዘግቡት ውጤት እየታየ ፕሮግራሙ እንደ አስፈላጊነቱ እየሰፋ እንደሚሄድ ያላቸውን ተስፋ አመላክተዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን 14 ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖችን እና ኢንዱስትሪ ፓርኮች በተለዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚያስተዳድር የመንግስት የልማት ድርጅት ሲሆን የተቀናጀ መሰረተ ልማትን በአንድ ቦታ ለባለሃብቶች በማቅረብ ባለሃብቶች ምንም አስተዳደራዊ ውጣ ውረድ ሳይገጥማቸው ባጠረ ጊዜ ወደ ስራ እንዲገቡ በማስቻል ሃገራዊ የኢኮኖሚ ሽግግርን ለማፋጠን የተቋቋመ ተቋም መሆኑ ይታወቃል፡፡