• +251118722266
  • Striving for eco industrial park
logo
  • by admin
  • 0Comments
  • 9 months ago
  • 312 Views

ዋና ስራ አስፈፃሚው ከወደብ ማግኘት ጋር ተያይዞ ያስተላለፉት መልዕክት

"የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለውን እንቅስቃሴ በእጥፍ የሚያሳድግ ነው" - አክሊሉ ታደሰ 

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አመራሮችና  ሰራተኞች የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ላይ ያተኮረ ወቅታዊ ሀገራዊ ውይይት አድርገዋል። 

የውይይት መድረኩን የመሩት የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ ኢትዮጵያ  የባህር በር ለማግኘት ያደረገችው ስምምነት የ120 ሚሊዮን ህዝብ የህልውና ጥያቄ እንጂ የቄንጥ ጉዳይ አለመሆኑን ገልፀው ኢትዮጵያ የባህር በር እጅጉን የሚያስፈልጋት፤ የሚገባትና  ለስኬታማነቱም በፅናት የሚቆም ህዝብና መንግስት ያላት ሀገር ናት ብለዋል። 

አቶ አክሊሉ በተጨማሪም የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ረጅም ጊዜ የፈጀ በሳል የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ውጤት መሆኑን ገልፀው የአካባቢውን ጂኦ ፖለቲካዊ አካሄድ በእጅጉ የቀየረና የመንግስት ከፍተኛ ቁርጠኝነት ያለው ውሳኔ በግልፅ የተንፀባረቀበት የታሪክ ምዕራፍ መሆኑን አረጋግጠዋል። 

ጉዳዩ እንደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ያለንን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥና የኢንቨስትመንት ፍሰቱን በከፍተኛ ሁኔታ የሚጨምር በመሆኑ ሁላችንም በፀና አንድነት በመቆም ለውጤታማነቱ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅብናልም ብለዋል። 

በውይይቱ የተሳተፉ የኮርፖሬሽኑ አመራሮችና ፈፃሚዎች በበኩላቸው የሀገርን እድገት ለማምጣትና የህዝቦቿን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ብሎም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለውን የተነቃቃ የገቢ ወጪ ንግድ ለማሳደግ የባህር በር ወሳኝ መሆኑን ገልጸው እንደ ህዝብ በህዳሴው ግድባችን ያሳየነውን ኢትዮጵያዊ አንድነት በመድገም ለትውልድ የሚተላለፍ ምንዳ ማስቀመጥ እንደሚገባ አንስተዋል። 

በዛሬው የኮርፖሬሽኑ ሀገራዊ ወቅታዊ ውይይት ላይ ከ300 በላይ የሚሆኑ የኮርፖሬሽኑ የስራ አመራር አባላት ፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ስራ አስኪያጆች ፤ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አገልግሎት አመራርና ሰራተኞች እንዲሁም የዋናው መሰሪያ ቤትና የቅርንጫፍ ሰራተኞች ተሳትፈውበታል።