"የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለሃገር እድገት የበኩሉን ሚና እንዲያበረክት በጥናት የተደገፉ ሳይንሳዊ ስራዎቻችንን አጠናክረን እናስቀጥላለን" ሽፈራው ሰለሞን
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሽፈራው ሰለሞን ይህን ያሳወቁት የኢንዱስትሪ ዘርፍ አምራች ማህበራት እና የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡
በውይይት መድረኩ መክፈቻ ንግግር ያደረጉት ዋና ስራ አስኪያጁ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አገልግሎት ለረጅም ዓመታት ያካበተውን የማማከርና አዋጭነት ጥናት የመስራት ልምድ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ላይ ለመተግበርና ከአምራች ማህበራቱ ጋር አብሮ በመስራት ውጤታማነታቸውን ለማረጋገጥ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ለአንድ ሃገር ኢኮኖሚ እድገትና ልማት መረጋገጥ የኢንዱስትሪ ዘርፉን መደገፍ ወሳኝ በመሆኑ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አገልግሎትም ለዘርፉ ስኬታማነት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልጸው ወደፊትም ዘርፉን መደገፍ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ አብረው ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊ የኢንዱስትሪ ዘርፍ አምራች ማህበራት በበኩላቸው ተቋሙ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ለመደገፍ ያሳየውን ተነሳሽነት አድንቀው ያለውን የካበተ ልምድ በመጠቀም በዘርፉ ያለውን ተግዳሮት ለመቅረፍ የሚያግዝ መሆኑንና ወደፊትም ከማህበራቱ ጋር በሚኖራቸው ትብብር ዘርፉን አንድ ደረጃ ለማሳደግ በጋራ ለመስራት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አገልግሎት ባለፉት 40 ዓመታት በማማከርና የአዋጭነት ጥናት በመስራት በዘርፉ ለሃገር እድገትና ልማት ትልቅ ፋይዳ ያላቸው ስራዎችን ያበረከተና ለበርካታ ተቋማትና የልማት ድርጅቶች ስኬት የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ላይ የሚገኝ አንጋፋ ልምድ ያለው ተቋም ነው፡፡