• +251118722266
  • Striving for eco industrial park
logo
  • by admin
  • 0Comments
  • 11 months, 3 weeks ago
  • 570 Views

የዋና ስራ አስፈፃሚው የምዕራብ አርሲ ዞን የመስክ ጉብኝት

"ዘላቂ የገበያ ትስስር የተፈጠረላቸው አርሶ አደሮች ህይወት በተጨባጭ እየተለወጠ መሆኑን  አረጋግጠናል" - አክሊሉ ታደሰ 

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ስር በሚተዳደሩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያሉ የግብርና ምርት አቀነባባሪዎች አማካኝነት ቋሚ የገበያ ትስስር የተፈጠረላቸው አርሶ አደሮች ህይወት እየተለወጠ መሆኑን በተጨባጭ አረጋግጠናል ሲሉ የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ ገለፁ። 

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ ይህን የገለፁት ከኮርፖሬሽኑ ስራ አመራር አባላት ጋር በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የቢራ ገብስ ብቅል ማቀነባበር ላይ ለተሰማራው ሱፍሌ ለተሰኘው የፈረንሳይ  ኩባንያ የቢራ ገብስ የሚያቀርቡ አርሶ አደሮችን በጎበኙበት ወቅት ነው። 

ዋና ስራ አስፈፃሚው ከኮርፖሬሽኑ ስራ አመራር ጋር ባደረጉት የመስክ  ጉብኝት በምዕራብ አርሲ ዞን በሚገኙት በሻሸመኔ ወረዳ ሁርሳ ቀበሌ እና በቆሬ ወረዳ ዶዳ ደዩ ልዩ ቀበሌ የሚገኙ አርሶ አደሮችን የጎበኙ ሲሆን አርሶ አደሮቹ በተፈጠረላቸው የገበያ ትስስር ተጠቃሚ እየሆኑ መሆኑን በመመልከታችን ደስተኞች ነን ብለዋል። 

ከማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው በተጨማሪ ኮርፖሬሽኑ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን የጠቁሙት አቶ አክሊሉ ለእነዚህ ኩባንያዎች የጀርባ አጥንት የሆኑ አርሶ አደሮች ተጠቃሚነታቸው መረጋገጡን በመመልከታችን ደስተኞች ነን ብለዋል። 

አርሶ አደሮቹ ከ60 ሺ ቶን በላይ ለቢራ ምርት የሚውል ገብስ በማምረት ሱፍሌ ለተባለ የፈረንሳይ ኩባንያ ግብዓት የሚያቀርቡ ሲሆን በዚህም ኢትዮጵያ የብቅል ምርትን ከውጪ ለማስገባት የምታወጣውን ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ በማስቀረት ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት እንዲሸፈን በማድረግ በኩል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ናቸው።  

ዋና ስራ አስፈፃሚው እንዳሳወቁት በቀጣይ በባህርዳር በአኩሪ አተር እንዲሁም በድሬዳዋ ከግመል ወተት የግመል የዱቄት ወተት ለሚያመርቱ ግዙፍ ኩባንያዎች ግብዓት የሚያቀርቡ አርሶና አርብቶ አደሮች ወደ ስራ እንደሚገቡ ይጠበቃል። 

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በቦሌ ለሚ ፤ በደብረብርሀን እና  በጅማ ገንብቶ በሚያስተዳድራቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሁም በቅርቡ በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና በግብርና ምርት ማቀነባበር ዘርፍ ለተሰማሩ ኩባንያዎች ግብዓት የሚያቀርቡ አርብቶ አደሮችን ጨምሮ ከ110 ሺ በላይ የሚሆኑ አርሶ አደሮች ዘላቂ የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸዋል።