በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በሚገኙ አምራቾች አማካኝነት ያገኘነው ገበያ ከህገወጥ ደላሎች ታድጎናል - የምዕራብ አርሲ ዞን አርሶ አደሮች
ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በሚገኙ የግብርና ምርት አቀነባባሪ ኩባንያዎች አማካኝነት በተፈጠረላቸው ዘላቂ የገበያ ትስስር ተጠቃሚ መሆናቸውንና ያለማቋረጥ ምርታቸውን እንዲያቀርቡ እንደረዳቸው የምዕራብ አርሲ ዞን አርሶ አደሮች ገልፀዋል።
አርሶ አደሮቹ ይህን የገለፁት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ከስራ አመራሮች ጋር በምዕራብ አርሲ ዞን በሚገኙት በሻሸመኔ ወረዳ ሁርሳ ቀበሌ እና ቆሬ ወረዳ ዶዳ ደዩ ቀበሌ የመስክ ጉብኝት ወቅት ነው።
አርሶ አደሮቹ በተፈጠረላቸው ዘላቂ የገበያ ትስስር ጥሪት እያፈሩ ፤ ህይወታቸው እየተቀየረ መሆኑን እና በመሀል ከሚገኙ ህገ ወጥ ደላሎች ወጥተው ምርታቸውን በቀጥታ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለሚገኙ ኩባንያዎች በማቅረባቸው ገቢያቸው ከፍ ማለቱን ይህም ከዚህ በበለጠ ስራቸውን አጠናክረው ለመቀጠል መነሳሳት እንደሆናቸው ገልፀዋል።
የኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ አመራሮች በማሳችን ተገኝተው እንዴት ስራችንን እየከወንን እንደምንገኝ ስለተመለከቱና ለቀጣይ ስራችን ስላበረታቱን ደስታችን ከፍ ያለ ነው ያሉት አርሶ አደሮቹ በቀጣይ በከፍተኛ ምርት ወደ ገበያው ለመቅረብ ጠንክረው እየሰሩ እንደሚገኙ አሳውቀዋል።
አርሶ አደሮቹ በአሁን ሰዓት በምዕራብ አርሲ ዞን በድምሩ በ90 ሺ ሄክታር መሬት ላይ ከ60 ሺ ሜትሪክ ቶን በላይ የሚሆን የገብስ ምርት በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለሚገኘው ሱፍሌት ለተሰኘው የፈረንሳይ ኩባንያ በቋሚነት እያቀረቡ ይገኛሉ።