• +251118722266
  • Striving for eco industrial park
logo
  • by admin
  • 0Comments
  • 1 year ago
  • 839 Views

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለሚሰሩ ዜጎች የጤና አገልግሎት

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለሚሰሩ ዜጎች የጤና አገልግሎትን ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ 

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከጤና ሚኒስትር፤ ከክልል ጤና ቢሮዎች እንዲሁም ከአጋሮች ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል። 

ስምምነቱም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰሩ ዜጎች የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ሲሆን ኢንዱስትሪ ፓርኮችም በተመጣጣኝ ዋጋ ለሰራተኞች የጤና አገልግሎት ማቅረብ እንዲችሉ ያግዛል ተብሏል። 

የሰነዶቹ መፈረም የኢትዮጵያ መንግስት ለቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበት መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በመድረኩ ያስገነዘቡ ሲሆን የስራው ባለቤት በዋናነት ክልሎች በመሆናቸው ትኩረት ሰጥተው በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ 

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኦፕሬሽንና ማኔጅመንት ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሚል ኢብራሂም በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው 13 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ80 ሺህ በላይ ወጣቶች የስራ እድል ማግኘት መቻላቸውን ጠቅሰው፤ እነዚህ ወጣቶች ተገቢውን የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ከጤና ሚኒስቴር እና የክልል ጤና ቢሮዎች ጋር ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡ 

በመድረኩ የክልል ጤና ቢሮ ሃላፊዎች፣ የኢንደስትሪ ፓርኮች ተወካዮች፣የሴቶች እና ማህበራዊ ሚኒስቴር ተወካዮች፣ የፌደራል ጤና ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎች፣ የአጋር ድርጅት ተወካዮች፣ ሲቪል ማህበራት እና የሚዲያ አካላት የስምምነት ሰነዶቹ በተፈረሙበት መድረክ የተገኙ ሲሆን የፓናል ውይይትም አካሂደዋል፡፡