• +251118722266
  • Striving for eco industrial park
logo
  • by admin
  • 0Comments
  • 11 months, 3 weeks ago
  • 397 Views

የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና

"የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና በሙሉ አቅሙ ስራ ለመጀመር የሚያስችል ቁመና ላይ ነዉ" - የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገብረመስቀል ጫላ የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና በሙሉ አቅሙ ስራ ለመጀመርና የሎጀስቲክስ የንግድ እና ሌሎች ከማኒፋክቸሪንግ ዘርፍ በተጨማሪ ያሉ የኢንቨስትመንት ዘርፎችን ለማስተናገድ የሚያስችል ቁመና እንዳለዉ ገልፀዋል።

ሚኒስትሩ የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና ዉስጥ የሚገኙና በተለያዩ የማኒፋክቸሪንግ ዘርፎች የተሰማሩ ሀገር በቀልና አለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ያሉበትን የምርት እንቅስቃሴ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ ጋር በመሆን ተመልክተዋል።

ሚኒስትሩ በምልከታቸዉም ኮርፖሬሽኑ የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠናን በአጭር ግዜ ዉስጥ ዉጤታማ ለማድረግና በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ እንዲገባ ለማድረግ ያከናወናቸዉ ስራዎች አበረታች መሆናቸዉን አንስተዋል።

አያይዘዉም ነፃ ንግድ ቀጠናዉ በስራ እድል ፈጠራ፤ ተኪ ምርቶችን በማምረት፤ በቴክኖሎጂና በእዉቀት ሽግግር ባለፈዉ አንድ ዓመት የደረሰባቸዉ አበረታች ዉጤቶች የሚደነቁ ናቸዉ ያሉት አቶ ገብረመስቀል በቅርቡ በሙሉ አቅሙ ስራ እንዲጀምር በሎጀስቲክስ በትሬድና በኢምፖርት ኤክስፖርት ዙሪያ የተደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች ተጠናክረዉ መቀጠል እንዳለባቸዉ አስታዉሰዋል። ለዚህም ሰሞኑን እየተካሄደ የሚገኘዉ የባለድርሻ አካላት ውይይት አይነተኛ ግብዓት እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና አሁን ላይ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ባለሀብቶችን እያስተናገደ የሚገኝ ሲሆን በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ወደ ተወካዮች ምክርቤት የተላከዉ የልዩ ኢኮኖሚክ ዞን አዋጅ ሲፀድቅ በንግድ፤ በሎጀስቲክስ፤ በኢምፖርት ኤክስፖርትና በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ባለሀብቶችን መቀበል ይጀምራል።