በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የኢትዮ ኮርያ ቴክስታይል ቴክኖ ፓርክ ተመረቀ
በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ በኢትዮጵያና ደቡብ ኮርያ ጥምረት የተገነባው የኢትዮ ኮርያ ቴክስታይል ቴክኖ ፓርክ ተመርቋል።
በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ሰለሞን በወንድማማችነት መንፈስ ለረጅም አመታት የዘለቀው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪያላይዜሽን ያድጋል፤ ለዚህም ኮርፖሬሽኑ ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዋል።
በሁለቱ አገራት የጋራ ጥምረት የተገነባው ፓርክ በጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የስልጠና፤ የላብራቶሪ አገልግሎትና አዳዲስ ጽንሰ ሃሳቦች ማመንጫ ማዕከል ሆኖ እንደሚያገልግል ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል ኮርያ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት አስፈላጊውን ድጋፍ ሰታደርግ መቆየቷ በመድረኩ የተጠቆመ ሲሆን የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ ለአፍሪካ ገበያ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር እንደሆነም ተገልጿል።
በመድረኩ የደቡብ ኮርያ ባለሞያዎች የኢትዮጵያን ኢንዱስትርያላይዜሽን ሊደግፉ ይችላሉ የተባለ ሲሆን የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የቴክኖሎጂ ሽግግር ፣አቅም ግንባታና የእውቀት ሽግግርን እንደሚፈጥርም ተጠቁሟል።