የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በአዳማ ከተማ በ100 ሚሊዮን ብር ለሚያስገነባው ትምህርት ቤት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከአዳማ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር በአዳማ ከተማ ቡኩ ሸነን ቀበሌ በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ ለሚያስገነባው ትምህርት ቤት የመሰረት ድንጋይ በዛሬው እለት ተቀምጧል።
የመሰረት ድንጋዩን የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ እና የአዳማ ከተማ ከንቲባ ሀይሉ ጀልዴ እንዲሁም የከተማው ከፍተኛ አመራሮች ከአባገዳዎች እና ከሀደ ሲንቄዎች ጋር በጋራ አስቀምጠዋል።
ኮርፖሬሽኑ በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ አማካኝነት የሚያስገነባው ትምህርት ቤቱ በተለያዩ የግንባታ ምዕራፎች ከቅድመ መደበኛ እስከ መሰናዶ የትምህርት ደረጃ የሚገነባ ሲሆን የስፖርት ሜዳ፤ የተማሪዎች ማረፊያና መዝናኛ፤ የአትክልትና አረንጓዴ ስፍራን በማካተት ለትምህርት ቤቱ አስፈላጊ የሚሆኑ የትምህርት መገልገያ መሳሪያዎች የሚሟሉለት መሆኑ ታውቋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ ግንባታው በታቀደለት ጊዜ በጥራት እንዲከናወን እንዲሁም የመጀመሪያው ምዕራፍ በአንድ ዓመት ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ እንዲሆን ኮርፖሬሽኑ አስፈላጊውን የድጋፍና ክትትል ስራ ያለማቋረጥ እንደሚያከናውን አሳውቀዋል።