• +251118722266
  • Striving for eco industrial park
logo
  • by admin
  • 0Comments
  • 12 months ago
  • 348 Views

የአፍሪካ የነፃ ንግድ ቀጣና

የአፍሪካ የነፃ ንግድ ቀጣና ተቀራራቢ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት የሚኖረው ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ

የአፍሪካ የነፃ ንግድ ቀጣና መመስረት የኢትዮጵያን ኢንዱስትሪ ፓርኮች የስራ እንቅስቃሴ ከማሳደግና የኢንቨስትመንት ፍሰትን በመጨመር ትልቅ ሚና እንደሚኖረው በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የማርኬቲንግና ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘመን ጁነዲ ገለፁ።

ኃላፊው ከሀገሬ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና አሁን ላይ በአህጉሩ እየጎለበተ የመጣዉን የአፍሪካዊ ወንድማማችነት (ፓን አፍሪካኒዝም) እሳቤ ይበልጡን በማሳደግ እርስበርስ የተደጋገፈ ተቀራራቢ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት ትልቅ መሰረት የሚጥል ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል።

ነፃ ንግድ ቀጣናው ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት በአፍሪካ ያላትን መሪ ተዋናይነት ይበልጡን የሚያጠናክር መሆኑን የገለፁት ኃላፊው በአህጉሩ በዘርፉ ይበልጥ ተወዳዳሪ ለመሆንና ተጠቃሚነታችንን ለማረጋገጥ የሚያስችል ስራ እየተሰራ ነዉ ብለዋል።

አክለውም በመሰረተ ልማት ግንባታ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናን በተለያዩ የትራስፖርት አዉታሮች ለማገኛት የተሰሩ ስራዎች የቅድመ ዝግጅቱ ማሳያ መሆናቸውን ያስታወሱት አቶ ዘመን ለአብነትም ኬኒያ ላሙ ደረቅ ወደብ ድረስ የሚዘልቀዉንና ወደ ደቡባዊ አፍሪካ የሚሻገረዉን የ ባቱ ሐዋሳ ሞያሌ የፍጥነት መንገድን ጠቅሰው ኢትዮጵያም በአገሪቱ የመጀመሪያ የሆነዉን የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣናን በማቋቋም በዘርፉ የበኩሏን ሚና በመጫወት ላይ ትገኛለች ብለዋል።

የአፍሪካ የነፃ ንግድ ቀጣና በቆዳ ስፋቱ ተወዳዳሪ የሌለዉ በአለም ላይ ቁጥር አንድ ግዙፉ ቀጠና ሲሆን ከ1.3 ቢሊዮን በላይ ህዝቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን ፤ በቀጠናው ኢትዮጵያ ያላትን ተጠቃሚነት በይበልጥ ለማስፋት የሚያስችሉ ተግባራት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በኩል በመከናወን ላይ እንደሚገኙ አቶ ዘመን ከቴሌቪዥን ጣቢያው ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልፀዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከዉጭ ምንዛሪ ግኝት ፤ ከተኪ ምርት እምርታ በተጨማሪ በዕዉቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ኢትዮጵያ በዘርፉ ለምታልመዉ መዋቅራዊ ሽግግር መሳካት የማይተካ አስተዋፆ በማበርከት ላይ መሆናቸውን የገለፁት ኃላፊው በተለይም ባለፉት 4 ዓመታት የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማነቃቃትና የግል ባለሀብቱን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች በመንግስት በኩል መሰራታቸውንና በዚህም ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።

የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና በአለም ትልቁ ነፃ የንግድ ቀጠና ሲሆን 54 የአፍሪካ ህብረት አገራትን እና 8 ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦችን ያካተተ ሲሆን ህብረቱ በአዲስ አበባ ባካሔደው 18ኛው መደበኛ ጉባኤ ላይ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና የመመስረት ስምምነትን አፅድቋል።