በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሠራተኞች ሁለገብ ኅብረት ሥራ ማህበር መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ማከፋፈያ መደብር እና የህፃናት ማቆያ ተመረቀ
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያስገነባው መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሰራተኞች የሚያቀርብ የሠራተኞች ሁለገብ የሸማች ኃላፊነቱ የተወሰነ መሰረታዊ ኅብረት ስራ ማህበርና ዘመናዊ የህጻናት ማቆያ አስመርቋል።
በምረቃ ስነ ስርዓቱ የተገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ሰለሞን ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለሀገር፣ ለሀዋሳ ከተማ እና ለአካባቢው ነዋሪዎች እያበረከተ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው ኮርፖሬሽኑ በፓርኩ የሚገኙ ባለሀብቶች የምርት ሂደት ላይ ብቻ እንዲያተኩሩና ሠራተኛውም ተረጋግቶ ሥራውን እንዲሰራ ለማድረግ በሁሉም ፓርኮች ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል ብለዋል።
አቶ ሽፈራው በተጨማሪም ለስራው መሳካትና ወደ ተግባር ለመገባቱ በፓርኩ የሚገኙ ባለሀብቶችን እና አስተዋፅኦ ያበረከቱ ባለድርሻ አካላትን አመስግነው በሌሎች ፓርኮችም በተመሳሳይ ወደ ስራ በመግባት እንደሚገኙ ገልፀዋል።
በምረቃ ስነ ስርዓቱ በስራው ለተሳተፉና አስተዋፅኦ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት የምስጋና የምስክር ወረቀት እና እውቅና የተሰጠ ሲሆን የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብርም ተከናውኗል።